የሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ ታሪክAba Pictureሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ ከአባታቸዉ ከአቶ ደምሴ ገብረ እግዚአብሔር እና ከእናታቸዉ ወይዘሮ አያልነሽ ይገለጡ ታኅሳስ ፩ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም በቀድሞ አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በተጉለትና ቡልጋ አዉራጃ በአንኮበር ወረዳ በዘንቦ ተክለ ሃይማኖት ቀበሌ ልዩ ስሙ ጓኝ በተባለ ቦታ ተወለዱ። የተወለዱበት ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ በጣሊያን የተወረረችበት ወቅት ስለነበረ በዚሁ ሳቢያ በትዉልድ ቦታቸዉ አካባቢ በተደረገ ጦርነት በአረመኔዎች እጅ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ በመሆኑ በሕፃንነታቸዉ ሰማዕትነት ተቀብለዋል ማለት ይቻላል። በኋላም ከትዉልድ ቦታቸዉ ከወላጅ እናታቸዉ ጋር ራሳ ወደ ተባለዉ አገር ተወስደዉ የሕፃንነት ጊዜአቸዉን በዚያ ካሳለፉ በኋላ በወጣትነት ደረጃ ሳሉ እንደ ገና ወደ ትዉልድ ቦታቸዉ ተመልሰዋል።

በትዉልድ ቦታቸዉ እያሉም በወቅቱ በዘንቦ ተክለ ሃይማኖት ተቀምጠዉ በማስተማር ላይ ከነበሩት ከአባ እሼቴ ወልደ ዮሐንስ ዘንድ ፊደል ቆጥረዉ፤ የንባብና የቃል ትምህርታቸዉን ቀጥለዋል። በ፲፱፻፵፯ ዓ/ም ወደ ኤቲሳ ደብረ ፅላልሽ ገዳም ሄደዉ ከየኔታ ተከሥተ በኋላም መልአከ ሰላም ተከሥተ ወ/እየሱስ ከተባሉት የቅኔ መምህር ዘንድ ገብተዉ ያቋረጡትን የንባብና የቃል ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ ዳዊት ደግመዉ ሥርአተ ቅዳሴ ተምረዉ እንደጨረሱ ወደ አዲስ አበባ መጥተዉ ክብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ማዕረገ ዲቁና ተቀብለዉ በዚሁ በኤትሳ ደብረ ፅላልሽ ገዳም በግብረ ዲቁና እየቀደሱ የቅኔ ትምህርታቸዉንም እየቀጠሉ ከቆዩ በኋላ እንደገና ወደ መንዝ ሄደዉ ዘብር ገብርኤል በሚባል ቦታ የኔታ አክሊሉ ወ/ማርያም ከተባሉ የፀዋትወ ዜማና የአቋቋም መምህር ዘንድ የቁም ዜማ ትምህርታቸውን ቀጥለዉ በሚገባ ተምረዋል። ከዚያም ወደ ደብረ ፅጌ ገዳም በመሄድ በዚሁ ገዳም ያስተምሩ ከነበሩት የኔታ ልዑል ዘንድ የመዝገብ ቅዳሴ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀዋል:: በዚሁ ገዳም እያገለገሉና እያስተማሩ ሳሉም በ፲፱፻፶፫ ዓ፡ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ባሉበት ስርዓተ ምንኩስና ፈፅመው ወዲያውኑ የቅስና ማዕረገ ክህነት ተቀብለዋል:: ከዚያም ወደነበሩበት ደብረ ፅጌ ገዳም ተመልሰው ገዳሙን እያገለገሉና በቅስናም እየቀደሱ የኔታ ቶማስ ከተባሉት የቅኔ መምህር ዘንድ የግዕዝ ሰዋሰውና የቅኔ ትምህርታቸውን ተምረዋል::

በ፲፱፻፶፮ ዓ፡ም ከደብረ ጽጌ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በመንበረ ፀባዎት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመንፈሳዊ አገልግሎት ተቀጥረው እያገለገሉ ዘመናዊ ትምህርታቸውን በዚሁ ካቴድራል በተቋቋመው ሥላሴ ት/ቤት የ፩ኛና መካከለኛ ፪ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በነገሌ ቦረና እና በአዲስ አበባም አስፋ ወሰን ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት ይባል በነበረው በኋላም ምስራቅ አጠቃላይ በተባለው ት/ቤት አጠናቀዋል:: ሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ በዚሁ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ለሰባት ዓመታት ያህል በቅስና ማዕረገ ክህነታቸው ሰፋ ያለ አገልግሎት ሰጥተዋል:: በሙዚየም ውስጥም የቅርሳ ቅርስ ኃላፊ ሆነው በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል። ከመንበረ ጸባዎት ቅድስት ሥላሴ ወደ ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ተዛውረው ለ፫ ዓመታት ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጥተዋል።

በ፲፱፻፷፮ ዓ/ም መጀመሪያ ላይ በጦር ሠራዊት ውስጥ ላሉት የሠራዊት አባላት በአበ ነፍስነት እንዲያገለግሉ ተቀጥረው በ፬ኛ ክፍለ ጦር ፬ኛ ብርጌድ ፳፯ኛ ሻለቃ ውስጥ ነገሌ ቦረና ሄደው እንዲያገለግሉ ተመድበው ሳሉም አገራቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን በቅንነት እና በጽኑ እምነት በሚገባ አገልግለዋል። በነዚህም አመታት ለሠራዊቱ ከሚሰጡት መንፈሳዊ የሆነ የአበ ነፍስነት አገልግሎት ውጭ በመጀመሪያ የነገሌ ቦረና ቅ/ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ቄሰ ገበዝ በኋላም የዚሁ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። አስተዳዳሪም ሆነው በሚያስተዳድሩበት ጊዜም ከሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍ ያለ ፍቅርና ተወዳጅነት በማግኘታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን ሠርተዋል። በዚሁ በነገሌ ቦረና በነበሩበት ወቅት የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የታወጀበት፣ የደርግ ባለስልጣናትና ተከታዮቻቸው እግዚአብሔርን የካዱበት፣ የሰው ልጅ ደም እንደ ውሃ የሚፈስበት አሰቃቂ ጊዜና ወቅት በመሆኑ ሊቀ ኀሩያን አባ ወልደ መስቀል ደምሴ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክራችሁን አንሱ ወይም የሰው ደም ማፍሰሳችሁን፣ ነፍስ መግደላችሁን አቁሙ” በማለት በአደባባይ በድፍረት ስለ ሰበኩና ሥርዓቱን ስለተቃወሙ በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ነጋዴዎች በዓብይ ጾም ያለውድ በግድ አርደው የሥጋ ምግብ እንዲያዘጋጁ ይደረግ ነበርና ይህንንም አጥብቀው በመቃወማቸውና በአደባባይ በማውገዛቸው ለ፭ ወራት በነገሌ ቦረና ከታሰሩ በኋላ ከቦረና ወደ አዋሳ ተወስደው ጦር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጎ ሳለ ምዕመናኑ ይልቁንም በዚያ የሚገኙት የጦር ሰራዊቱ አባላት የመንፈስ ልጆቻቸው ስለ እሳቸው መታሰር ድርጊቱን በግልጽ በመቃወማቸው አምስት ዋስ እንዲጠሩና እንዲለቀቁ ተጠይቀው ዋስ አልጠራም ያለበደል ታስሬአለሁና ከእስር ቤትም አልወጣም በማለታቸው በእሳቸው ምክንያት ችግር እንዳይከሰት ሲባል አንድ ዋስ ብቻ ጠርተው እንዲለቀቁ ተደርገዋል።

በመጨረሻም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያሉ ካድሬዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት ብዙ ፈተና ስለአደረሱባቸው በአበ ነፍሥነት ስራ ምድብ ሆነው የሀዋርያነት ተግባር መፈጸም በማይቻልበት ደረጃ ላይም በመድረሳቸው ጦር ሠራዊቱን ተሰናብተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ፫ኛ ፓትርያርክ ፈቃድ በትንሳኤ ማሳተሚያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የመጻሕፍት መጋዘን ሓላፊ ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል። ቀደም ሲልም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ኃይማኖት የሰአሊተ ምሕረት ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው የሾመአቸው ሲሆን የሹመት ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ እሳቸው ትምህርት ቤት ገብተው መማርን ስለመረጡ አሁንም በፓትርያርኩ ፈቃድ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ገብተው በመማር የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን አጠናቀው በ፲፱፻፹፪ ዓ/ም በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን አጠናቀው በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ውስጥ የመጻሕፍትና ልዩ ልዩ ህትመቶች ስርጭት ክፍል ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ ተመድበው ሥራቸውን በጥንቃቄና በፍጹም ታማኝነት እየሰሩ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፹፬ ዓ/ም ለመንፈሣዊ አገልግሎት ወደ ስዊድን ተልከው በእስቶኮልም ከተማ በመድኃኔዓለም ስም የተመሰረተችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በቅን ልቦና እና በትህትና ሲያገለግሉና ለምዕመናንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በኋላም መለያየትና መከፋፈል እየጎላ በሚመጣበት ጊዜ እሳቸው ሲኖዶስ የሚባለው በአዲስ አበባ በመንበረ ፓትርያርክ ያለው ሲኖዶስ እንጂ ስደተኛ ሲኖዶስ የሚለውን አልቀበልም፤ በጸሎትም መጠራት ያለባቸው በዚያው በቦታው በመንበሩ ያሉት ቅ/ፓትርያርክ መሆን አለባቸው የሚል ጽኑ ዓላማ ስላላቸው በዚህ ምክንያት በተነሳው አለመግባባት ደጋፊዎቻቸው ምዕመናንን ይዘው ከተቃዋሚዎች ተነጥለው በቅድስት ሥላሴ ስም በዛው በእስቶኮልም ከተማ ቤተ ክርስቲያን ኣቋቁመው አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል። ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ በዚሁ በስዊድን ሳሉ በአውስትራልያ፣ በጀርመን፣ በፊላንድ፣ በኖርዌይና በዴንማርክ እየተመላለሱ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።

በመጨረሻም ወደ ካናዳ ቫንኮቨር ሄደው የቫንኮቨር ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን እና በቪክቶሪያ ደሴት ላይም የመንበረ ብርሃን ዳግማዊ ቁልቢ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አቋቁመው የሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ሆነው ለአምስት አመታት አገልግለዋል። ቀጥሎም ስራው እየሰፋና አገልግሎቱ እየበዛ በመሄዱ ለቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሌላ አገልጋይ ካህን አስመደቡ። እሳቸው የኆኅተ ሰማይ ማርያም እና በዚያ የሚገኙትን ምዕመናን በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ ሲያገለገሉ ቆይተዋል። እንደ ስዊድን ሁሉ ተቃዋሚዎች በካናዳ ቫንኮቨር ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በእጃቸው ለማስገባት ፈተና ቢያበዙባቸውም እሳቸው ምዕመኑን በማስተማርና በማጠናከር በምዕመናኑም ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት የተነሳ በእግዚአብሔርም አጋዥነት ቤተ ክርስቲያኒቱን በስደት ካሉ አባቶቸ ወደ ገለልተኝነት በመቀጠልም የአንዲት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አካል እንድትሆን አድርገዋል።

በመጨረሻ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከሕመማቸው መፈወስ ባለመቻላቸው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሄደው ጸበል በመጠመቅና በመጠጣት ፈውስ ማግኘት ስለፈለጉ ምዕመናኑ ከፍተኛ የአሸኛኘት ፕሮግራም አዘጋጅተው ከሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔም ሀገረ ቤት የሚያደርሳቸው ሰው ተመድቦ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት እንባ በእንባ በመራጨት የክብርና የአባትነት አሸኛኘት አድርገውላቸው ጳጉሜ ፪ ቀን ፳፻፫ ዓ/ም ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ወደ ቅድስት ሃገራቸው ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮም በጸበል እና በሕክምና እየተረዱ ቆይተዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፤ የዓለም ዓብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ከብጹዓን ለቃነ ጳጳሳት ጋር ከአረፉበት ቤት ድረስ በመሄድ አባታዊ ቡራኬ ከመስጠታቸውም በላይ ሰፋ ያለ ግዜ ወስደው አጽናንተዋቸዋል አበረታተዋቸዋልም::

ሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ በሰው ሁሉ ፊት ትህትናን የተላበሱ ቸር፣ በኃይማኖት ጉዳይ ችግር ሲያጋጥማቸው ግን ማንንም የማይፈሩ ፍጹም ደፋር የነበሩ መንፋሳዊ አባት፣ እግዚአብሄርን የሚፈሩና የሚያፈቅሩ፤ ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትሩ፤ ሰዎችንም የሚያከብሩና ከፍቅረ ነዋይ የራቁ፤ በአጠቃላይ ለሰዎች እንጂ ለራሳቸው ኖረው የማያውቁ፤ ፍጹም ታማኝ የእግዚአብሄር ሰው ነበሩ። ነገር ግን ዕድሜያቸው በመግፋቱና ፈተና ስለሆነ ሕመማቸው ስር የሰደደ ሆኖ ከቀን ወደ ቀን እየበረታባቸው በመሄዱ በአዲስ አበባም እንደገና ወደ ተለያዩ ሀኪም ቤቶች ገብተው በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ከዚህ ከሀላፊው ዓለም ተለይተው ዘለዓለማዊ ዕረፍትን አርፈዋል። ዕረፈታቸው እንደታወቀም ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተወስደው ሥርዓተ ፍትሀት ሲደረግላቸው ካደረ በኋላ ጥቅምት ፲፬ ቀን ጧት በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸዉ ባሉበት ፀሎተ ፍትሐት ተደርጎ በመልካም አሸኛኘት ተሸኝተዉ ሥርዓተ ቀብራቸው በዚሁ ዕለት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል።

እግዚአብሔር አምላካችን የአባታችንን ነፍስ ከቅዱሳን ይደምርልን፤ በረከታቸው ይደርብን።


የወንጌል፡ገበሬ፡አባ፡ወልደ፡መስቀል፡
አርሰው፡አለስልሰው፡የዘሩት፡አዝመራ፡
ከኢትዮጵያ፡ስዊድን፡
ሰሜን፡አሜሪካ፡ቫንኮቨር፡ጎመራ፡፡
ስራቸው፡ይኖራል፡ለትውልድ፡ሲያበራ፡
ዘወትር፡ከኛ፡ጋራ፡
ይህ፡የመንፈስ፡ስራ፡፡

ሊቀ ኅሩያን፡ቆሞስ፡አባ፡ወልደ፡መስቀል፡ደምሴ፡በኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ባጭሩ፡እንዴት፡ይታወሳል?

በ፳፻፮ ዓ.ም (እ.አ.አ.) በቫንኮቨር፡ቤተ-ክርስቲያን፡ተከስቶ፡በነበረው፡መከፋፈል፡ወላፈን፡ላይ፡በመገኘት፡መንጋውን፡ከተኩላ፡የሚታደግ፡ታዳጊ፡እረኛ፡አጥቶ፡በመበተን፡አደጋ፡ላይ፡የነበረውን፡ምዕመን፡በአምላካችን፡እና፡በፈጣሪያችን፡ እግዚአብሄር፡ቸርነት፡ከመበተን፡እና፡ከመጥፋት፡አደጋ፡ታድገውታል፡፡ በተለይ፡በወቅቱ፡ከነበረው፡ምዕመናን/ናት፡ህሊና፡ጨርሶ፡ሊፋቅ፡የማይችለው፡ድርጊት፡ተከስቶ፡የነበረው፡በጥምቀት፡በዓል፡ቀን፡ነበረ፡፡ ዕለቱ፡በጣም፡ብርድና፡ቀዝቃዛ፡ነበረ፡መቼም፡የቫንኮቨርን፡ቅዝቃዜ፡ለሚያውቅ፡ሰው፡ለቀባሪው፡አረዱት፡እንዳይሆንብኝ፡እሰጋለሁ፡፡በዋዜማው፡ሲወርድ፡ያደረው፡በረዶ፡በአንዳንድ፡ቦታዎች፡የመኪና፡ጎማዎችን፡ይሸፍን፡ነበረ፤ ከነዚህም፡ቦታዎች፡አንዱ፡በወቅቱ፡የምንገለገልበት፡ፓተርሰን፡የሚባለው፡ቦታ፡ነበረ፡፡

በማግስቱ፡እሁድ፡ሊቀ፡ኅሩያን፡በዓለ፡ጥምቀትን፡ለማክበር፡ማልደው፡ ወደ፡በተክርስቲያን፡ይሄዳሉ፤ በወቅቱ፡የጠበቃቸው፡ግን፡የተለየ፡ነገር፡ነበረ። አስቀድሞ፡ህዝበ ክርስቲያኑን፡ለመበታተን፡ሴራ፡ያጠነሰሰው፡ዲያቢሎስ፡በተደራጀ፡መልኩ፡ተዘጋጅቶ፡የቤተክርስቲያኑን፡በር፡በመያዝ፡አላስገባም፡አለ፡፡ ሊቀ ኅሩያን፡የፍቅር፡አባት፡ግን፡ለሰይጣን፡ሴራ፡ቦታ፡ሳይሰጡ፡በትዕግስት፡በቆራጥነትና፡በእግዚአብሄር፡ኃይል፡በመታገዝ፡ባሳዩት፡ጥንካሬ፡የሰይጣንን፡ሴራ፡አሸንፈው፡በዓሉ፡እንዲከበርና፡መንገድ፡ዳር፡ቆመው፡በጥርጣሬ፡ይመለከት፡ለነበረው፡ምዕመንም፡የብርሃን፡ችቦ፡ሆነው፡በሃይማኖት፡ፀንቶ፡በቤተክርስቲያን፡እንዲኖር፡አርዓያ፡ሆነውልናል፡፡

በ፳፻፱ ዓ.ም (እ.አ.አ.) ደግሞ፡በቤተክርስቲያን፡ላይ፡ተደቅኖ፡በነበረው፡የመከፋፈል፡አደጋ፡ወቅትም፡በጾም፡በጸሎት፡በመታገዝ፡ምዕመኑን፡በፍቅር፡በትዕግስትና፡በአንድነት፡በመያዝ፡ሐዋርያት፡በሰበሰቡዋት፡በአንዲት፡ቅድስት፡ቤተክርስቲያን፡እና፡በአንድ፡ሲኖዶስ፡ጥላ፡ስር፡እንዲቆይ፡አድርገዋል፡፡

ሊቀ ኅሩያን፡በህይወታቸው፡ዘመን፡የነበራቸው፡ህልምና፡የገዘፈ፡ምኞታቸው፡ኢትዮጵያዊ፡ወገናቸው፡የራሱ፡የሆነ፡መሰባሰቢያ፡ቤተክርስቲያን፡እንዲኖረውና፡ኦርቶዶክሳዊ፡የተዋህዶ፡መስቀል፡ያለው፡ህንጻ፡ተገንብቶ፡እውን፡ሆኖ፡ማየት፡ነበረ፡፡ ከዚህ፡ዓለም፡በህይወተ፡ስጋ፡እስከተለዩበት፡ዕለትም፡ድረስ፡ስለ፡ሰው፡ልጅ፡የነበራቸው፡ፍቅርና፡ርህራሄ፡በእኛ፡በልጆቻቸው፡ልብ፡ውስጥ፡ዘወትር፡ሲታወስ፡ይኖራል፡፡

“እኔ፡ሰውን፡ሁሉ፡እወዳለሁ፡ሰው፡ግን፡ይወደኛል፡ብዬ፡አስቤ፡አላውቅም” ህመሙ ጠንቶባቸው ወደ ኢትዮጵያ፡በተሸኙበት፡ወቅት፡ከተናገሩት፡ የተወሰደ ሲሆን ከዚህ፡የምንማረው፡በእግዚአብሄር፡አምሳል፡የተፈጠረውን፡ፍጡር፡ሰውን፡መውደድ፡እንዳለብን፡ነው፡፡

የመጨረሻ፡ምክራቸው፡-

“አንድ፡ሰው፡፲፪፡ልጆች፡ነበሩት፡ልጆቹን፡ጠርቶ፡አንድ፡አንድ፡እንጨት፡እንዲያመጡ፡አዘዘ፡ ቀጥሎም፡የተሰበሰበውን፡እንጨት፡እንዲያስሩት፡አደረገና፡ከእናንተ፡አንዳችሁ፡ስበሩት፡አላቸው፡ማናቸውም፡እስሩን፡መስበር፡አልተቻላቸውም፡በመቀጠልም፡ዕሥሩን፡እንዲፈቱት፡አዘዘና፡ስበሩት፡አላቸው፡እንጨቱንም፡ በቀላሉ ሰበሩት፡፡ አባታቸውም፡ልጆቹን እንዲህ፡አላቸው፡”በመካከላችሁ፡መለያየትን፡አስወግዳችሁ፡በአንድነት፡ብትቆሙ፡እንዲሁ፡ትጠነክራላችሁ፡ከተለያያችሁ፡ግን፡እንዲሁ፡ትጠፋላችሁ፡፡”

ሊቀ ኅሩያን እኛንም፡እንዲህ አሉን፡”ልጆቼ፡መለያየትን፡አስወግዳችሁ፡መስማማትን፡መከባበርን፡በፍቅር፡መኖርን፡ግን፡አጥብቃችሁ፡ውደዱ፡እግዚአብሄርም፡ከእናንተ፡ጋር፡ይሆናል፡፡”

አሜን፣ የአባታችን በረከታቸው ይደርብን።
ወስብሃት፡ለእግዚአብሄር፡ወለ፡ወላዲቱ ድንግል፡ ወለ፡መስቀሉ፡ክቡር፡
ኃይለ፡ማርያም፡
ከኆኅተ ሰማይ፡ ቫንኮቨር-ካናዳ
ጥር ፲፩ ፣፳፻፭ ዓ.ም.