የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ

(Board of Directors)

የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ምንድነው? በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ያለውስ ድርሻ ምን ይመስላል? የሚሉትን ከማንሳታችን በፊት በቅድሚያ ስለቤተ ክርስቲያን አመሰራረት፣ ስለቤተ ክርስቲያን መስፋፋትና ስለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ታሪካዊ አመጣጥ በአጭሩ እንመለከታለን።
የቤተ ክርስቲያን መሠረት

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በገዛ ደሙ በዋጃት ቤዛም በሆናት በሕያው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሐዋ፤ ፳፡ 28)። ሲመሠርታትም በሐዋርያት ትምህርት (ስብከት) እና በነቢያት ትንቢት ላይ ነው (ኤፌ፤ ፪፡ ፳)። ለዚህም ነው የሐዋርያትን አለቃ ቅዱስ ጵጥሮስን፡ “ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” (ዮሐ፤ ፳፩፡ ፲፭) ሲል የጠባቂነት ሥልጣን እንደሰጠው በሕያው ቃሉ የተነገረው። ዳግመኛም ስለ ቤተ ክርስቲያን መሠረት “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም። የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” (ማቴ፤ ፲፮: ፲፰) በማለት የሰጠው ቃል ኪዳን ዋና ምስክር ነው።

ከላይ በተገለጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የተነሳ እኛ ክርስቲያኖች “ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሠሯት (በሰበሰቧት) በአንዲት ቅድስት (ክብርት) ቤተክርስቲያን እናምናለን” እያልን ዘወትር በሃይማኖት ጸሎት ስንናገር እንኖራለን፤ እንዲሁም የክርስቶስ አካል የሆነችውና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸችው ቤተክርስቲያንም አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት መሆኗን በፍጹም እምነት እንመሰክራለን።

የቤተ ክርስቲያን መስፋፋት

በመጀመሪያይቷ ቤተ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት (ክርስቲያኖች) እየበዙ ሲሄዱ የቤተክርስቲያን መሥፋት፣ የወንጌል ቃል መዳረስ መልካም ሆኖ ሳለ ነገር ግን መላውን አማኞች (ምእመናን) በእኩልነት ለማስተዳደር የሚያስችል መዋቅር ባለመኖሩ ችግር ተፈጥሮ ነበር። አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሏቸው። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን። ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላባቸውን ሰባት ደቀ መዛሙርት፦ እስጢፋኖስ፣ ፊልጶስ፣ ጵሮኮሮስ፣ ኒቃሮና፣ ጢሞና፣ ጳርሜና፣ ኒቆላዎስን መርጠው በሐዋርያት ፊት አቆሟቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጭነው ሾሟቸው (ሐዋ፤፮፡ ፩-፯)። እነዚህም የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ማለትም የመጀመሪያዎቹ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ናቸው (ቃለ ዓዋዲ ገጽ ፩)።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ከዘመነ ሐዋርያት ጊዜ ጀምሮ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ዜና ወንጌል ተሰበከ እንጂ የተደራጀ ክህነታዊ አገልግሎት አልነበረም። ሆኖም በዚሁ ወቅት በቅዱሳን ሐዋርያት እንደተመሠረቱት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ኢየሩሳሌም በተሰበሰበው የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ በተላለፈው ቀኖና እና ሲያያዝ በመጣው የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጻሕፍት ትተዳደር ነበር።

በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት በኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭ ዓ.ም.) የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና ፫፻፲፰ ሊቃውንት (ሠለስቱ ምዕት) ከሐዋርያት ሲኖዶስ ሲያያዝ የመጣውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርገው ለቤተክርስቲያንና ለሀገር አስተዳደር እንዲጠቅም ብለው ፍትሐ ነገሥት የተሰኘውን የሕግ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለንጉሡ ለቆስጠንጢኖስ ሰጡት። ፍትሐ ነገሥት ሥርወ ቃሉ ግዕዝ ሲሆን ቃል በቃል ሲፈታ የነገሥታት ፍርድ ማለት ነው። ይኸውም ክርስቲያን ነገሥታት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን የሚያስተዳድሩበት ወይም ፍርድ/ፍትሕ የሚሰጡበት የሕግ መጽሐፍ ነው። ከታላቁ ቆስጠንጢኖስ ጀምሮ ክርስቲያን ነገሥታት ፍትሐ ነገሥትን ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ማስተዳደሪያ ሕግ አድርገው መጠቀም ጀምረዋል። በሀገራችን በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭) አፈ ጉባኤ በነበረው በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹሞ ወደ አክሱም ሲመጣ ፍትሐ ነገሥትን ጨምሮ ብዙ የሥርዓት መጻሕፍትን ይዞ ስለመጣ አብርሃ ወአጽብሃ (ነገሥታተ ኢትዮጵያ) ሀገሪቷንም ቤተ ክርስቲያኒቷንም በፍትሐ ነገሥት ያስተዳድሩ ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአብርሃ ወአጽባሃ ዘመነ መንግሥት ከአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (፫፻፴ ዓ.ም.) ጀምሮ በቅርብ ጊዜ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (፲፱፻፵፱ ዓ.ም.) የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በሥራ ላይ እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ወደ ፩ሺ፮፻ ዓመታት ያህል ሀገሪቱም ሆነች ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚመሩበት ሕግ ፍትሐ ነገሥት (ፍትሕ መንፈሳዊና ፍትሕ ሥጋዊ) ነበር።

ቃለ ዓዋዲ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. ለቤተ መንግሥት ከተዘጋጀ ከ16 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ኅብረት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንድትደራጅ ታስቦ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና በትእዛዝ አዋጅ ቁጥር 85/65 ተፈቅዶ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. በሥራ ላይ ዋለ።ቃለ ዓዋዲ የሚለው ሐረግ መሠረተ ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ቃል በቃል ሲፈታ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ማለት ነው። ይኸውም በነቢያት ትንቢት የተነገረውን (ኢሳ፤40፡3) ኋላም የጌታን የመምጣቱን አዋጅ እየተናገረ በመጣው በመጥምቁ ዮሐንስ የተፈጸመውን (ማቴ፤3፡1-17) የንስሐ ጥሪ፣ የመንግሥተ ሰማያት አዋጅ መሠረት አድርጐ የተሰየመ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አዋጅ ነው። አንድ መንግሥት ሕዝቡን የሚያስተዳድርበት በግልጽ በአዋጅ የሚነገር ሕግ አለው። እንደዚሁ ሁሉ ቃለ ዓዋዲም በምድር የእግዚአብሔር ቤተ መንግሥት የሆነች፣ የመንግሥተ ሰማያት በር፣ የሰማይ ደጅ የምትባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ዜጐቿ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚተዳደሩበት የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ሕግ ነው። ይህም ዋናውን የእግዚአብሔር ሕግ (ወንጌለ መንግሥትን) መሠረት በማድረግ ለዘመኑ በሚበጅ መልኩ የተዘጋጀ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ሕግ ነው። ስለዚህ ቃለ ዓዋዲ በኋላ ዘመን የተፈጠረ ሳይሆን የቤተክርስቲያን አመራርና አስተዳደር በኢየሩሳሌም በተደረገው የሐዋርያት ጉባኤ (ሐዋ፤15፡32) ተመክሮና ተወስኖ በተላለፈው ሕግና ሥርዓት በማኅበረ ካህናቱና ምእመናኑ ጠቅላላ ጉባኤ በተመረጡ ቅዱስ መንፈስ ባደረባቸው ኃላፊዎች (ሐዋ፤6፡1-7) ሥራ አስፈጻሚነት ይካሄድ የነበረውን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው (ቃለ ዓዋዲ ገጽ 1)። ይህ ቃለ ዓዋዲ (የቤተክርስቲያን አስተዳደር አዋጅ) ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ሳይለቅ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ እንደጊዜው ሁኔታ ሚያዚያ 19/1970፣ ታህሣሥ 10/1974፣ ግንቦት 9/1977፣ ግንቦት 10/1991 ተሻሻሏል።

የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋት አገልጋዮቿን መዝግባ ይዛ ሥምሪት እና ምደባ ለመስጠት፣ ችሎታቸውንና ኑሮአቸውን ለማሻሻል፣ ምእመናንን ለማብዛትና በመንፈሳዊ እውቀት ጎልምሰው፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማሻሻልና በሚያስፈልጋት ማንኛውም ጉዳይ ራሷን ለማስቻል ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ በየደረጃው የሚቋቋም የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ መዋቅርና አሠራር በቃለ ዓዋዲው መሠረት ዘርግታ ትገኛለች፡፡ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤዎች በሕዝብ በሚመረጡ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና አስፈላጊ የሆነውን አቅም ለማጐልበት የሚመክርባቸው፣ የሥራ ክንዋኔዎችና ችግሮች እየቀረቡ የሚገመገሙባቸውና ልምዶች የሚወስዱባቸው፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችም እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሚል የሚታይባቸው ናቸው። በ1991 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 61 /2/ /ሀ/ ላይ የሰበካ ጉባኤ የሚኖረውን የምእመናን ድርሻ በተመለከተ፡- ”የሰበካ ምእመናን በገንዘብ አስተዋጽኦ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በልማትና በማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎት በጠቅላላው በሀብት፣ በዕውቀትና በጉልበት በመርዳት በሰበካው ልዩ ልዩ የክፍል ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ነው” በማለት በተደነገገው መሠረት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሲሰጡ ለሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ መሳካት ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡

የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንም ቃለ ዓዋዲውን መሰረት በማድረግና የምንኖርበት ክፍለ ሀገር ህግ (BC Society Act) በሚያዘው መሰረት የተቋቋመች ስለሆነ በየሁለት ዓመቱ በጠቅላላ ጉባዔው በሚመረጡ ከካህናት፣ ከምዕመናንና ከሰ/ት/ቤት በተውጣጡ ሰባት የሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ትመራለች። የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤውም ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን የሚከተሉት የስራ ክፍሎች አሉት፡
፩ኛ) የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት (የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ ም/ሊቀ መንበርና ጸሐፊውን ያቀፈ)
፪ኛ) የማህበራዊ ጉዳዮችና ስፖንሰርሽፕ ማስተባበሪያ ክፍል
፫ኛ) ገንዘብ ቤት
፬ኛ) የንብረትና ሂሳብ ስራዎች ማስተባበሪያ ክፍል
፭ኛ) የሰንበት ት/ቤት ማስተባበሪያ ክፍል
በነዚህ ክፍሎች ስርም እንደየስራው አስፈላጊነት በርካታ ኮሚቴዎች ተቋቁመው እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህ አወቃቀርም ምዕመናን በችሎታቸው በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሳተፍ እንዲችሉ የሚያደርግ ሲሆን ዳር ቁመን የምንመለከተው ወይም እገሌ ይሠራዋል፤ በሚል ልንሸሸው የማይገባ፣ ተሳታፊ በመሆን በረከት የምናገኝበት እና የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚቀረፍበት መዋቅር ነው፡፡ በመሆኑም የሚጠበቅብንን የድርሻችንን ካልተወጣንና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን በወቅቱ ካላደረግን ደንቡና መዋቅሩ ብቻውን ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል በተሰጠን ጸጋ ልናገለግል ይገባል፡፡ እግዚአብሔርም ከእኛ ብዙ ይጠብቃል፡፡ የተቀበልነው መክሊት ነውና በተሰጠን መጠን ይፈለግብናል /ማቴ. 25-14-30፡፡

አሁን በማገልገል ላይ ያሉት የሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላትብፁዕ አቡነ ማትያስ የምዕራብ ካናዳ ሃገር ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሊቀ ማዕምራን ቆሞስ አባ ዕዝራ አማረ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ፤ ሊቀ መንበር
አቶ በላይ ገለቱ ም/ሊቀ መንበር
ዶ/ር በላይ ጋጋ ዋና ጸሐፊ
ወ/ሮ ራሄል ኮርሴ የሰንበት ት/ቤት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ
አቶ ብርሃኑ ተክሉ የማህበራዊ ጉዳዮችና ስፖንሰርሽፕ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ
አቶ ሲሳይ አምባቸው የንብረትና ሂሳብ ስራዎች ማስተባበሪያ ክፍል
አቶ ጌታቸው ግርማ ገንዘብ ያዥወስብሃት ለእግዚአብሔር!