የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ዲያቆናት

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የገባው ቃል ኪዳን በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ፣ ብቸኛና ፍጹም በሆነ ክህነቱ መስዋዕት አቅራቢ ካህን፣ መስዋዕት ተቀባይ አምላክ፣ ራሱም እውነተኛ መስዋዕት በመሆን አዳነን፤ ከበሽታችን ፈወሰን፤ ሞታችንን ሞቶ የትንሣኤ ሕይወትን ሰጠን። በዚህም አጥተነው የነበረው ጸጋችን ተመለሰልን፣ አዲስ ሕይወትም ተሰጠን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የፈጸመው የማዳን ሥራ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ላሉ ምዕመናን እንዲደርስ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተልን። እነዚህን ምሥጢራት በክርስቶስ ክህነት የሚፈጽሙ አባቶች በአንብሮተ ዕድ፣ በንፍሐተ መንፈስ ቅዱስ ሾመልን። ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው ”መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” እንዲል። ዮሐ. ፳፡ ፳፪-፳፫። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም። የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” (ማቴ ፲፮፥፲፰) ብሎ ስልጣነ ክህነትን ሰጠው። ኃላፊነቱንም እንዲህ በማለት አደራ አስረከበው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” ጌታችን ኢየሱስም “በጎቼን ጠብቅ አለው”። ዳግመኛም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” “ጠቦቶቼን አሰማራ አለው።” ሦስተኛ ጊዜም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን? ስላለው ተከዘ። “ጌታዬ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” “እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው።” ዮሐ. ፳፩ ፦ ፲፭ - ፲፯። በጎች የተባሉ ለጊዜው ሀዋርያት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላው መምህራንን ጠብቅ ማለቱ ነው። ጠቦቶች የተባሉ ለጊዜው ሰባ ሁለቱ አርድዕት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላውን ጠብቅ ማለቱ ነው። ግልገሎች የተባሉ ለጊዜው ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላውን ጠብቅ ማለቱ ነው።

የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የክህነት አገልግሎት ዋና ይዘት ፍቅር፣ ራስን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ መስጠት መሆኑን አሳየን። ከጌታችን የባሕርይ ምንጭነት የተገኘው የአዲስ ኪዳን ክህነት ሐዋርያትን አረስርሶና አርክቶ በቂ የሆነ ክህነታዊ ተግባርም አሳይቶ አሁን ባሉ አባቶች ላይ ይገኛል። አምላካቸውን ያገኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽማቸው ምሥጢራት ስላሏት፣ ምሥጢራቱ የሚፈጸሙትም የግድ በካህናት ስለሆነ ክህነት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አስፈላጊና የማይቀር ነው። ይህም በዓለም ያለው በእግዚአብሔር አርዓያና ምሳሌ የተፈጠረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንዲያይበትና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝበት ነው።

ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በነሐሴ ወር ፲፱፻፹፮ ዓ. ም. (August 1994) በወቅቱ በነበሩ ጥቂት ምዕመናን ተመሰረተች። ስትመሰረት በአካባቢው ምንም ካህናትና ዲያቆናት ስላልነበሩ ከቶሮንቶና ከሲያትል አባቶች ካህናት አልፎ አልፎ እየመጡ ይቀድሱና ለህዝቡም ቡራኬ ይሰጡ ነበር። እንዲሁም ደግሞ ከኤድምንተንና ከካልጋሪ ወንድሞች እየመጡ ወንጌል ሲያስተምሩ ቆይተዋል። የሌለው እንዳለ እየታሰበ ያለካህን በቴፕ ቅዳሴ እያስቀደሱና እርስ በእርሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ እየተማማሩ ወጣት መዘምራንም በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የቤተክርስቲያኗን ህልውና ይፈታተኑ የነበሩትንም መናፍቃን እየተጋፈጡ የሚያጸና አምላክ አጽንቷቸው ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ ለደረሰችበት ትልቅ ደረጃ እንድትበቃ ታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርገዋል። በእንደዚህ ሁኔታ የተመሰረተችው የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቸርነት በአሁኑ ሰዓት በሙሉ ልዑክ ካህናት አገልግሎት ይሰጥባታል። የተገልጋዮች ምዕመናን ቁጥርም እንዲዚሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ በየሳምንቱ እስከ ፪፻ ምዕመናን የሚገበኙባት ታላቅ ደብር ለመሆን በቅታለች።

በሌላ በኩል ደግሞ በዓመታዊ የንግስ በዓላት ወቅት የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ማትያስ፣ የቪክቶሪያ ዳግማዊ ቆልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ የሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናት እየመጡ ያገለግላሉ። በዓመት እስከ አራት ጊዜ ያህል ካናዳና አሜሪካ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ካህናትን/መምህራንን በመጋበዝ ለተወሰነ ጊዜ እየቆዩ ምዕመናንን ወንጌል እንዲያስተምሩ በመደረግ ላይ ነው። ይህ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን መንፈሳዊ አገልግሎትና እየጨመረ የሄደውን የካህናትና የምዕመናን ቁጥር እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ ይጠብቅልን።

በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ካህናትና ዲያቆናት በፎቶው ላይ የሚታዩት ናቸው።
ከግራ ወደ ቀኝ፦ ዲ/ን ዶ/ር አበራ ደመቀ፣ ዲ/ን ነብዩ ሳሙኤል፣ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ኃይለ ልዑል አካሉ፣ ዲ/ን ፍሬዉ ዘገየ፣ ቆሞስ አባ እዝራ አማረ፣ ቀሲስ ዶ/ር ዳንኤል ነጋሽ፣ ዲ/ን ዘላለም ጎበና