የሙዳዬ ምጽዋትኮሚቴ
(Mudaye Mitswat)

አሥራት በኩራት ማውጣት አምላካዊ ሕግ ነው!

እግዚአብሔር ለሰው መጠቀሚያ ምድር የምታፈራውን ሁሉ የሰጠው ሲሆን፤ ሰው ግን አምላክ ከሰጠው ከፍሎ ጥቂቱን መስጠት ይሰስታል። ሰው ሠርቶ ሲያገኝ ለምድራዊ መንግሥት ግብር ባይከፍል የሚደርስበትን ሁሉም ያውቀዋል። በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ ፲፬ ቁጥር ፳፪-፳፭ ያለውን ብንመለከት “ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ፤ ሁልጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ሥፍራ በአምላክ በእግዚአብሔር ፊት” ይለናል የእግዚአብሔር ቃል (ሕግ)።

ሰው ሀብት የሚያገኘው በተፈጠረበት ምድር አድጎ መሥራት ሲችል ነው። ለዚህም ኢዮብ እንዲህ ይለናል “የሰው ልጅ ወደ ዓለም ሲመጣ ራቁቱን ይመጣል፤ ዓለምን ተሰናብቶ ሲሄድም ራቁቱን ይሄዳል” ኢዮብ ፩፡ ፳። ስለዚህ የሰጠንን እንዲባርክልን የእሱን በሕጉ መስጠት ተገቢ ነው። በበለጸጉት አገራት ግብር ከፋይ መሆን ኩራት ነው፤ ይህም ገንዘብ ለሀገር ልማት ስለሚውል ነው። የእግዚአብሔርንም ላዘዘው ስናውለው የመንፈስ እርካታ ይሰጣል። ዘፍጥረት ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፪-፰ን ብንመለከት የአቤል እውነተኛ መስዋዕት ወንድሙን አስቀናውና “እግዚአብሔርም ቃየልን አለው ለምን ተናደድህ ለምንስ ፊትህ ተቋጠረ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅህ ታደባለች” ይህ ጥያቄስ ለእኛ አይመጣ ይመስለን ይሆን? ከሆነ ተላላነት ነው። ስለዚህ ስንሰጥ መስጠት ብቻ ሳይሆን ስንሰጥም በደስታ እግዚአብሔር የሚቀበለው መሆን ይገባዋል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛው ቆሮንቶስ ምዕራፍ 9 ቁጥር ፮-፱ “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ያጭዳል፣ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ያጭዳል እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና። እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይሁን፣ በሐዘን ወይም በግድ አይደለም….”ይላል። እንዲሁም ዳዊት በመዝሙረ ዳዊቱ ፵፱ ቁጥር ፰-፲፫ “እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ የእሱ እንደሆነ ዓለም በሙሉ የራሱ እንደሆነ … ለእግዚአብሔር የምስጋናን መስዋዕት ሠዋ ለልዑልም ስዕለትህን ሰዋ በመከራ ቀን ጥራኝ አደርግህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ ይላል የእግዚአብሔር ቃል”።

ያዕቆብ እንዲህ ይለናል፤ ዘፍጥረት ምዕራፍ ፳፰ ቁጥር ፳፪ “እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል ለሀውልት የተከልኩት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል። ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጣለሁ”ብሎ ሲያስተምረን አሥራት በኩራቱን የማይሰጥ ሰው እግዚአብሔርን እንደሰረቀ ይቆጠራል ብሎ የሚያስተምረን ነቢዩ ሚልኪያስ በምዕራፍ ፫ ቁጥር ከ፯-፲ ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል እርሷንም አልጠበቃችሁም ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ። ሰው እግዚአብሔርን ይሠርቃልን? እናንተ እኔን ሠርቃችኋል እናንተም ምንድነው የሠረቅንህ ብላችኋል፤ አሥራት በኩራት ነው። አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ በረከትንም አትረፍርፌ ባልሰጣችሁ በዚህ ፈትኑኝ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር”።

ቤተ ክርስቲያንን ለመሥራት መመረጥን ይጠይቃል፤ እስቲ ማነው እንኳን በእግዚአብሔር በሰው ሹም መመረጥን የማይፈልግ? ቅዱስ ዳዊት ለእሱ ባይፈቅድለት የቤተ መቅደሱን መሥሪያ ለልጁ ሰሎሞን እንዲሰጠውና እንዲሠራው አምላኩን የጠየቀበትን መጽሐፍ ቅዱስ ፩ኛ ዜና መዋዕል ምዕራፍ ፳፱ ቁጥር ፲፮-፲፱ እንደተጠቀሰው “አቤቱ አምላካችን ሆይ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ በእጅህ የመጣ ነው ሁሉም ያንተ ነው። አምላክ ሆይ ልብን እንድትመረምር ቅንነትንም እንድትወድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህንን ሁሉ አቅርቤያለሁ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንደቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ፣ ይሠራ ዘንድ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው” ብሎ አምላክን እንደለመነው ሁሉ እኛም ቤቱን ሠርተን ከእዳ ነፃ እንድናደርግለት ቃላችን አንድ ይሁን።

በሐዲስ ኪዳንም ብዙ ምሳሌ ማንሳት የሚቻል ሲሆን ሁለቱን በዋናነት እንጥቀስ፤ ዘኪዎስ የተባለው ሀብታም ቀራጭ ጌታ ወደቤቱ በገባ ሰዓት የተናገረውን ወንጌላዊው ሉቃስ ምዕራፍ ፲፱ ቁጥር ፩-፲፪ እንደጻፈ፤ ዘኪዎስ ለጌታ አለ “ጌታ ሆይ ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ … ሲለው ጌታም ዛሬ በዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና አለው” ይህ ነው መዳን ማለት። ሌላም ታላቅ ምሳሌ የምትሆነን ወንጌላዊ ማርቆስ ምዕራፍ ፲፪ ቁጥር ፵፩ እስከ መጨረሻው በተገለፀው አንዲት መበለት ሕዝብ ሁሉ መዋጮ ሲያወጣ እሷ ያላትን በሙሉ ከሙዳየ ምፅዋቱ ስትጥል ጌታም ለሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው “ብዙ ባለጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፣ አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ ፪ ዲናር ጣለች። እውነት እላችኋለሁኝ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋል ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ሁሉ፤ ትዳሯን ሁሉ ጣለች አላቸው። ከነዚህ የምንማረው አብልጦ መስጠት የበለጠውን ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን ነው።

የተወደዳችሁ ምዕመናን የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንም ከላይ በሰፊው እንደተገለጸው ሃይማኖታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ህግን በጠበቀ መልኩ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ያህል አሥራታቸውን በአግባቡ እንዲያወጡና ለሙዳዬ ምጽዋትም እንዲያበረክቱ ታሳስባለች። በየሳምንቱ እሁድና በበዓላት ወቅት ከቅዳሴ በኋላ እና እንዲሁም ልዩ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ሲኖር ከጉባኤ በኋላ ምዕመናን ኪሳቸው ያፈራውን በመለገስ የበረከቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ጃንጥላ ይዞራል። ይህንንም የሚያመቻች ፫ አባላት ያሉት የሙዳዬ ምጽዋት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል። የዚህ ኮሚቴ ዋና ተግባራትም ጃንጥላ በማዞር ከምዕመናን መባ መሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ መቁጠርና በዕለቱ የተገኘውን ለምዕመናን በማሳወቅ ለቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ ያዥ በደረሰኝ ገቢ ማድረግ ናቸው። ስለዚህ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር በመስጠት በበረከት እንድንሞላ እራሳችንን እናዘጋጅ፤ ለፈጣሪም ታማኝ እንሁን። ለዚሁም ፈጣሪያችን ቀና መንፈስና ንጹሕ ልቦና እንዲሰጠን እና በረከቱም እንዳይለየን እንለምነው።

የኮሚቴው አባላት ከግራ ወደ ቀኝ: ፩ኛ) አቶ በረከት መንግስቱ ፪ኛ) አቶ ጌትነት ሰብስቤ ፫ኛ) አቶ አብርሃም ለታ

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!