የንብረት አስተዳደር ኮሚቴ

ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶቿን በአግባቡ ለመፈጸም እንዲረዳት ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን ትጠቀማለች። መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጸምባቸው ዕቃዎች ከተባረኩ በኋላ ተለይተው ስለሚያዙና ስለሚቀመጡ ንዋያተ ቅድሳት ይባላሉ። ንዋያተ ቅድሳት የሚቀመጡት ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲሆን የሚንከባከቧቸውም ካህናት አባቶችና ዲያቆናት ናቸው። የንብረት አስተዳደር ኮሚቴ ከካህናት ጋር በመመካከር ንዋያተ ቅድሳትን ያሟላል፣ መታጠብ ያለባቸውን ልብሰ ተክህኖ (አልባሳት) እንዲታጠቡ ያደርጋል፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትን እንዲወገዱ ያደርጋል። በተጨማሪም በአጠቃላይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አገልግሎት የሚሰጡ የወጥ ቤትና የመጸዳጃ ዕቃዎች በየጊዜው እየተከታተለ በግዥ ወይም በስጦታ እንዲሟሉ ያደርጋል፣ በአግባቡ መቀመጣቸውን ያረጋግጣል። የንብረት አስተዳደር ኮሚቴ ሦስት አባላት ያሉት ሲሆን ተጠሪነቱም በሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ለሂሳብና ንብረት ክፍል ነው።