የመንፈሳዊ ጉዞ ኮሚቴ

“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ“ (መዝ ፻፳፪፥ ፩)

ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ“ እንዳለው የእግዚአብሔር ቤት- የቅድስናው ሥፍራ የበረከት ምንጭ የደስታ መፍለቂያ ነው። ወደ እግዚአብሔር ቤት ሒዶ መከፋት የለም። ስለሆነም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ቅዱሳት መካናት መንፈሳዊ ጉዞዎችን ማድረግ የተለመደ ነው። ከመንፈሳዊ ጉዞ ዓላማ ዋና ዋናዎቹ፤ በዕለቱ ከሚከበረው መንፈሳዊ በዓል በረከት ለማግኘት፣ ቅዱሳት መካናትን በመሳለም ከመካናቱ ከሚገኘው በረከትና ከተሰጣቸው ቃል ኪዳን ለመሳተፍ፣ የቅዱሳት መካናትን ቅርስና ታሪክ ለማወቅና ለመንከባከብ፣ በመንፈሳዊ ጉዞዎች ላይ በሚሰጡ ትምህርቶችና ውይይቶች መንፈሳዊ ሕይወትን ለማጠንከር ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ አቅም በፈቀደ ቅዱሳት መካናቱን በገንዘብና ቁሳቁስ መደገፍ በመንፈሳዊ ጉዞ ከሚከናወኑ ደገኛ ተግባራት አንዱ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የመንፈሳዊ ጉዞ ማስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ዓላማ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን በምታዘጋጀው መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሳተፉ በመቀስቀስና በማስተባበር ከመንፈሳዊ ጉዞው በረከት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። የኮሚቴው ዋና ዋና ሥራዎችም፡-

  • በተመረጡ ዓበይት በዓላት ለምእመናን መንፈሳዊ ጉዞዎችን ማቀድ፣ ማዘጋጀትና ማስፈጸም፣
  • ስለጉዞው ለአባላት በቂ መረጃ መስጠት፣
  • ለጉዞ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን (መጓጓዣ) ማሟላት፣
  • በጉዞ ላይ የሚከናወኑ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ማስተባበር ናቸው።

አሁን በማገልገል ላይ ያሉት የኮሚቴው አባላት ከግራ ወደቀኝ፡ በላይ ከበደ፣ ሙሉ ንጉሤ፣(በፎቶው ላይ የማይታዩ) ትግስት ንዋይ፣ ያዕቆብ ሉልሰገድ፣ ዶ/ር ደረጀ አሸብር ናቸው
እግዚአብሔር የምናስበውን ጉዞ ያሳካልን!