Articles
- የአደራ ቃል
- ያደረግነው ማተብ
- የምሕረት ቃል ኪዳን የተሰጠሽ እናት
- መልካም ሰርቶ ማለፍ
- የአባ ወልደመስቀል አለብን አደራ
- በቤቱ እንድንኖር ምርጫችን አንድ ይሁን
- ሰላም ለኪ ማሪያም
- የነበርን ዓይተናል
የአደራ ቃል
ሰርጾ ገብቶ የማይታይ
ክብረት ያለው ታላቅ ሲሳይ
የአባት ህልሙ እንዲፈፀም
ሻማ አብርቶ ተንበርክኮ የሚፀልይ
እንደ ሰዓት ጊዜ ቆጥሮ የሚደውል
የሚቁላላ እንደ ምግብ የሚበስል
ወተት ሆኖ የሚረጋ የሚመስል
የቆሞሱ የአባታችን የሆነ ቃል
ሄዶ ሄዶ ቆምኩኝ ይላል
ተስፋ ሳይቆርጥ ተመልሶ ይቀጥላል
የኸው እስከ ዛሬ ይናገራል
ኪሊል…. ኪሊልል…. ኪሊልል
እንደ ስልኩ ያንቃጭላል ይደውላል
አዎ! የአደራ ቃል
በትዝታ ስናያቸው
እንዲህ ነበር ገጽታቸው
እንዲህ ነበር ተግባራቸው
በክህነት አለባበስ በዚያ አባት ቁመና ከመቅደሱ ይቆማሉ
አሃዱ አብ ሊሉ
ፈጣሪ ሲመሰገን ሲጠሩ መላዕክት
ነብያት ሐዋሪያት
ስትወደስ የብርሃን እናት
ወንጌል ሲነበብ ብሉይ ከሐዲስ
አቤት እግዚኦ ማረነ ክርስቶስ
ፀናፅሉ ሲወዛወዝ ይታየኛል
ቅዱስ ዕጣን ይሸተኛል
ታምረ ማሪያም ይሰማኛል
ይኸ ነበር ተለምዷችን ሰንበት ሰንበት
በኦርቶዶክስ ሥርዓት ቆሞሱን ማየት
በወንጌል ትምህርት ድምፃቸውን መስማት
ዓይኔ ዛሬ ምን ነክቶታል
የልማዱን ማየት ተስኖታል
ጆሮስ ምነው? ምን ሆነሃል
የአባት ድምጹ የአባት ቃሉ ርቆሃል
ስንቱ ሕፃን ተጠመቀ በቆሞሱ
ስንቱ ታዳጊ ስንቱ አዋቂ ቆርቦ ነበር በቆሞሱ
አስከሬንም ተሸኝቷል እስቲ አስታውሱ
የአብርሃም የሣራ ብለው ቀድሰዋል
ሙሽሮችን በአባትነት መርቀዋል
እመጫቱን በየቤቱ ጠይቀዋል
ፀበሉንም ረጭተዋል
እስረኛንም አፅናንተዋል
ሁሉን እነዳመሉ አስተናግደው
ቁጭ ብድግ ብለው
የአባት ወጉን አሳይተው አስተምረው
ካህናት አፍርተው አብዝተው
አዲስ ትውልድ አደቁነው
ኢትዮጵያዊ ሙሴ ሆነው
ተፋቀሩ ይቅር ተባባሉ
ሥጋ ወደሙ ተቀበሉ
ቤተ ክርስቲያንን አገልግሉ
ነበረ ምክራቸው የዘወትር ቃላቸው ትዝ የሚለኝ ከሰማሁት
እናንተም የማትረሱት
የታሪክ ቅርስ የምታደርጉት
ኦርቶዶክስን የምታወርሱበት
ወንጌል የምትማሩበት የምታስተምሩበት
ፈጣሪን የምታወድሱበት
ድንግልን የምትማፀኑበት
በረከት የምታገኙበት
ደስታ ሃዘን የምታስተናግዱበት
የእኛ ነው የምትሉት
መቅደሱን ሥሩላት
ልጆቼ! ይብቃን ይህ የኪራይ ቤት
ነበር ያሉት ደግመው ደጋግመው ያሳሰቡት
ለሁላችን ያደራ ቃል የሰጡት
ልብ ያለው ልብ ይበለው
ትዝታው የቅርብ ነው
የቴፑን ቅዳሴ በእውን የቀየሩ
ታቦት አምጥተው ከመቅደስ ያኖሩ
ፍቅርን አቀብለው ፀብን ያባረሩ
የሁላችን አባት
መስቀል ይዘው ሻማ ያበሩ
የአደራ ቃል ለእኛ ትተው እሳቸው ሄደዋል
ዳግም ላናያቸው ርቀዋል
ሩጫውን በድል ጨርሰዋል
ሩጫውን በድል ተወጥተዋል
መንግስተ ሰማይ ያውርስልን
ጌታ በቀኝ ያቁምልን
የእሳቸው ረድኤት አይለየን
እኛንም የአደራቸው ቃል ፈፃሚ ያድርገን
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ጌታሁን ዘውዴ ወ/ኪሮስ
ያደረግነው ማተብ
ያኔ ገና! ገና ያኔ! በአርባ እና ሰማንያ በጨቅላ ዕድሜያችን
መሠረት የጣልነው ለዛሬው እምነታችን
ጣታችንን ለሰው ማተብ ከጌታችን
ዋጋ የተከፈለለት ደም የፈሰሰለት
ፀጋውና ፍቅሩ ማተብ ያረፈበት
ከአምላካችን ጋራ ከእመብርሃን ጋራ የተሳሰርንበት
በስሙ ኦርቶዶክስ፤ ክርሰቲያን ተብለን የተሰየምንበት
በጨቅላነት ዕድሜ ያደረግነው ማተብ
እስከአሁን ለኖርነው ሆኖልናል ቀለብ
በተወለድንበት በአደግንበት አገር
እንደየ አጥቢያችን በቀረበን ደብር
ማተቡን አድርገን ማስቀደስ ስንጀምር
ቃሉን እየሰማን ስንማር ስንዘምር
ገጠርም ይሁን ከተማ ለኖርነው
በድህነት ይሁን በድሎት ላደግነው
ጌታችንም ያው ማተቡም አንድ ነው
ከእኛ የሚፈለገው ልባችን ማፅናት ነው
የሕይወት ጉዞአችንን ዛሬ ላይ ለማድረስ ብዙ አታግሎናል
በአየርና ባሕር ስንት አገር ደርሰናል፤ ስንት አገር ዓይተናል
በእግራችንም ቢሆን ድንበር ተሻግረናል
መከራና ችግር በሽታውም ቢሆን ተፈራርቆብናል
የማተቡ ኃይል ግን ሁሉንም አስችሎ ጠብቆ ይዞናል
በጨቅላነት ዕድሜ ያደረግነው ማተብ
እስከአሁን ለኖርነው ሆኖልናል ቀለብ፤
ከእኛ ሕጻናቶች ምስጋናችን ይድረስ ለአንተ ለፈጣሪ
ወደአንተ እንድንመጣ ለአደረከው ጥሪ
ታላላቆቻችን እንዳይከለክሉን ስላደረክልን
አቅመቢስ ሆነን ጉልበት ስለሆንከን
በኮልታፋ አንደበት እግዚአብሔር ተመስገን
ወጣቶች ከሆነው ! እግዚአብሔር ተመስገን
ቀድሞ ስለመራን መልካሙን ጎዳና
እሱን እንድናምን አድርጎናልና
ቤቱ እየመጣን እንድናገለግል
ጉልበቱን ከጤና አብዝቶ ሰጥቶናል
እግዚአብሔር ይመስገን ለዚህ አድርሶናል
ጐልማሳ ለሆነው ሰዓቱን ጠብቆ ሁሉን ስለሰጠን
በትዳር መኖሩን ፤ ዘር መተካቱን
የሥራ ዕውቀቱን እንዲሁም ሹመቱን
ለወገን መቆርቆር ቤተሰብ መርዳቱን
እግዚአብሔር ለዚህ ስላበቃን
አዛውንት ስለሆን ! ይመስገን ! ተመስገን!
አልፋና ኦሜጋ ህያው እግዚአብሔር
ለዚህ ላበቃኸን ለንስሐ ክብር
የዕድሜ ባለጸጋ ላደረከን በምድር
ለታሪክም ቢሆን ሆነናል ምስክር
በጨቅላነት ዕድሜ ያደረግነው ማተብ
እስከአሁን ለኖርነው ሆኖልናል ቀለብ
የማርያምን ቤቷን ለመሥራት ብላችሁ
እስከዛሬ ድረስ በተባረከ እጅ ዳቦ የጋገራችሁ ቆሎ የቆላችሁ
በሰከነ ሙያ ሻይና ቡናውን ያፈላችሁ እንጀራና ወጡን ያበሳሰላችሁ
በመልካም ሁኔታ ያስተናገዳችሁ
በልዩ ችሎታ ጠላውን ጠምቃችው ጠጁን የጣላችሁ
በበዓል ዝግጅት ትኬቱን ቲ_ሸርቱን ጫማውና ልብሱን
ለስላሳና ውኃ,,,,,,ሌላም ሌላም ሌላም በመሸጥ ገቢ ላስገኛችሁ
በጥሬዉም ቢሆን ገንዘብ የሰጣችሁ
ልዪ ልዪ ነገር ስጦታ ያመጣችሁ
በጉልበትም ሳይቀር ጽዳት ላፀዳችሁ
ሙዳዩ ምፅዋት ጥላ ላዞራችሁ
በቲያትር ድራማ ለተሳተፋችሁ
በኮሚቴ ሥራ ጊዜ ለሰዋችሁ
ከቅጽራችን ውጪ በአገር ልጆች መሃል በተለያየ ጊዜ ድንኳኑን ተክላችሁ
ኆኅተ ሰማይን ምሰሶ አርጋችሁ
ከጠዋት አንስቶ እዚያው የዋላችሁ
በደጀን በመሆን ድጋፍ የሰጣችሁ
በመግዛትም ቢሆን የተባበራችሁ
ማተቡ ነውና ለዚህ ያበቃችሁ
የብርሃን እናት በረከቱን ሁሉ አብዝታ ትስጣችሁ
የልባችሁን መሻት ትፈጽምላችሁ
ከዚህ በተለየ! የቆሙሱን ተግባር ውርስ የወረሳችው
ሥርዓት እንዳይጐል ስላደረጋችሁ
እንድንባረክም አባቶች ጋብዛችሁ
በአዘኑም ቦታ እየተገኛችሁ
መጽናናት እንዲኖር ስላደረጋችሁ
የታመመውንም በመጠየቃችሁ
በደስታውም ቦታ ትምህርት የሰጣችሁ
አባቶች ዲያቆናት በሁሉም ሥፍራ ላይ ያገለገላችሁ
ጤናና ዕድሜውን ጽናትና ብርታት አንድዬ ይስጣችሁ
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ጌታሁን ዘውዴ ወ/ኪሮስ
የምሕረት ቃል ኪዳን የተሰጠሽ እናት
ወላዲተ አምላክ ቅድስት ወብፅዕት
በምሕረትሽ ጎብኝን ኪዳነምሕረት
በተሰጣት ኪዳን ቃል በገባላት
አማልዳ ስታስምር በጣም ፈጣን ናት
የፍጥረት አማላጅ የአንድዬ እናት
ፈጥና ትደርሳለች ከልብ ካመኗት
መዓዛ ፍስሃ ማህደረ መለኮት
በዓሏ ሲከበር በዛሬዋ ዕለት
ለኛም እንድትደርስ ነይ ነይ እንበላት
ጎዶሎ ህይወት ነው እሷ የሌለችበት
የተዋህዶ ልጆች የምንመካብሽ
ጸጋና በረከት የምናገኝብሽ
የወርቅ መሰላል ዕጸ መድሃኒት ነሽ
የወይን ሐረግ ነሽ የህይወት መሰላል
በዕምነቱ የጸና በምልጃሽ ይድናል
በምልጃሽ እንድንድን ለዓለም መጽናኛ
ከአምላክ የተሰጠሽ የሰው ልጅ መዳኛ
የጭንቅ አማላጇ እንደ በላየ ሰብ ድረሽልን ለኛ
ቃላቶች ያጥሩኛል ስለ አንቺ ስናገር
የዓለሙ መድህን ነሽና ማህደር
የዓለም ቤዛ ነው የማህጸንሽ ፍሬ
ክብርሽን አልዘልቅም ዘርዝሬ ዘርዝሬ
ልጅሽ መድሃኒት ነው እሱ አይሳሳትም
ከኛ ይጎድላል እንጂ ከሱ ጎድሎ አያውቅም
በዓለም ስንጓዝ ቢገጥመን ፈተና
በቤቱ እንድንኖር ፍጹም እንድንጸና
ንስሃን ሰጥቶናል መሀሪ ነውና
መስገድ ይገባናል መጸለይ በትጋት
ከቤቱ እንዳንወጣ እስከ ዕለተ ሞት
አነሳሽ እግዚአብሔር ፈጻሚም እሱ ነው
አልፋና ወሜጋ ምስጋና ይድረሰው
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ስንዱ ተድላ
መልካም ሰርቶ ማለፍ
የትኛውን ጽፌ የቱንስ ልተወው
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እስቲ ልጀምረው
አባ ወልደ መስቀል በህይወት ዘመናቸው
ቅዱስ፣ ቅዱስ ብለው እንደአባቶቻቸው
ለነፍሳቸው ያደሩ ታላቅ አባት ናቸው
ለነፍሳቸው ያደሩ ሐዋርያም ናቸው
ለምንድነው ሞት ሁሌ አዲስ የሚሆነው
በተራ እንደምንሄድ ከቶ እያወቅነው
ይመስለኛል ሞትማ አዲስ የሚሆነው
እንደ እኔ በሃጢያት ለወደቅነው
በንስሃ ታጥበን ላልተዘጋጀነው
ዛሬም ነገም ሁሌም አዲስ ነው
አባታችንማ ሆነው ይታዩኛል የመድሃኔዓለም ሙሽራ
በስውር የሰሩት ታላቁ ስራቸው በሰው ፊት አበራ
እኔ በራሴ ወስኛለሁ አላለቅስም በእውነት
እኚህ ክቡር ቅዱስ ለሆኑ አባት
በዚህ ቀን እሞታለሁ አላሉ አባቶች በተሰበሰቡበት
ስራቸውን ሊገልጽ መድህነ ዓለም የኛ አባት
ይህ ሁሉ ምስክር ነው ለኛ ለቆምነው በህይወት
እኛም ልጆቻቸው በዚህ ዘመን
የአባታችንን አደራ ተቀብለን
ህልም የሆነባቸውን መስቀሉን አቁመን
በንስሀ ታጥበን ለክብሩ እንዲያበቃን
የፍቅር ባለቤት ክርስቶስን ይዘን
ስለሌላው ሃጢያት መወንጀሉን ትተን
መጾም መጸለዩ ያ ነው የሚጠቅመን
ሁሉ ከንቱ ከንቱ ስራችን ብቻ ነው እኛን የሚያድነን
ሐዋርያው ጳውሎስ ሩጫዬን ጨረስኩ እንዳለው
ከልጅነት እስከመጨረሻው ምዕራፍ ለሃይማኖት ቆመው
አንድ ሁኑ ይቅር ተባባሉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈው
እረፍታቸው በተክልዬ ገዳም ሆነ ሩጫቸውን ጨርሰው
የዘመኑ ሰማዕትነት አባቶች እንደሚሉት
ራስን መሆን ነው ክርስቲያንነት
እንዳንወድቅ እንድንጸና በሃይማኖት
ጸሎትና ጸጋቸው አይለየን የአባታችን በረከት
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ስንዱ ተድላ
የአባ ወልደመስቀል አለብን አደራ
በህብረት አሰባስቦን ስንጀምር ፀሎት
ሁላችን አስታውሰን ያንን የመከራ የችግሩን ሰዓት
ማለፉ ደስ ብሎን ክበር ንገስ አልነው የአለምን መድሃኒት
እዚህ አድርሰውናል እንዳባቶቻችን ተጋድለው በእውነት
እንጸልያለን በደካማ አንደበት እንዳይለዩ ፍጡነ ረድኤት
እዚህ ስንመጣ ወደእግዚአብሔር ቤት
የተሰበረ ልብ ይዘን ባንድነት
እንጹም እንጸልይ እስቲ እንወቅበት
አይቀር መጠራቱ ተራ አለን ሁላችን እንሄዳለን ድንገት
ምን ይሆን ስንቃችን የሠራነው ሥራ
ለምታልፍ ዓለም ለበስባሽ ስጋችን ስንሮጥ እንደአሞራ
ለነብስ የምንለው ምን አቆይተናል ኋላ ስንጠራ
ክርስቲያን ወገኔ እስቲ አሁን እንንቃ ዛሬ እንመካከር
እርግፍ አድርገን ትተን ጥላቻ ቅያሜ እርስ በርስ መናቆር
እናስታውሰው ጌታ ያስተማረንን ወርዶ ወደምድር
ምንም አንጎዳ እስቲ እንከተለው እንኑር በፍቅር
በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማያዊው ቤት ይሆነናል ክብር
በአምላካችን አምሳል ተፈጥረን በአርአያው
ክብሩን እንድንወርስ አድርጎን ህያው
አባታዊ ፍቅሩን ማጣጣም አቅቶን
ከአለሙ ተባብረን ሃጤአታችን ከብዶን
የጥፋት ደመና አንዣቦብን ሳለን
አርነት አወጣን ፍቅሩን አለበሰን
ታምነን እንሰማራ በእምነት ጎዳና
ከቤቱ እንመገብ ሰማያዊ መና
ብርሃናችንን በሰው ፊት እናብራ
በመንገዱ እንገዝ መልካም ፍሬ እናፍራ
የድንግል ማርያምን ቤቷን እንድሰራ
የአባ ወልደመስቀል አለብን አደራ
የፍጥረቱን እዳ በደሉን ሊሽከም
ቀራንዮ ዋለ ሃያል መድሃኒዓለም
እናስተውል ሰዎች የተዋለልንን
ከሞት እንድንድን አምላክ የሰጠንን
ምክንያት ሳንደረድር ሳናበዛ ሰበብ
ንስሃ እንግባና ወደማእዱ እንቅረብ
ሂዱና አስተምሩ ብሎ እንደላካቸው ጌታ ሃዋርያትን
ምሳሌ ሆነዋል በስደት አገር ላይ እኝህ አባታችን
አባት የሌለው ልጅ ዲቃላ እንዳንባል
በትምህርት መልሰው ሙሉ አድርገውናል
አባ አባታችን አምላክ በቸርነት የለገሳቸው ሃብት
ትዕግስት ማስተዋልን ልብሳቸው አርገዋት
በረዶውን አልፈው አዚህ አደረሱን በእግዚአብሄር ቸርነት
ሰለጠንን ብለን እየሰየጠንን አባትን መዳፈር መናገር አምጥተን
ያንን ሁሉ ታግሶ አምላክ በቸርነት ለዚህ አደረሰን
እዛች ቅድስት አገር ጸበሏን ሲጠጡ
እንጸልያለን ድነው እንዲመጡ
አባ ወልደመስቀል ትጉህ አባታችን የሃይማኖት መሪ
ድነው ያገናኘን ቸርነቱ አያልቅም ሃያል ነው ፈጣሪ
አነሳሽ እግዚአብሄር ፈጻሚም እሱ ነው
አልፋና ኦሜጋ ምስጋና ይድረሰው
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ስንዱ ተድላ
በቤቱ እንድንኖር ምርጫችን አንድ ይሁን
የክርስትና ህይወት የኛ መንገዳችን
ልቤ ተነክቶብኝ በጣም አዘንኩና
ብዕሬን አነሳሁ በስመ አብ አልኩና
ካህናት መምህራን ዘወትር ሲያስተምሩን
ህይወት የሆነውን ወንጌል ሲመግቡን
ውሃና እሳቱ ለይተው ሲነግሩን
በሳት መቃጠሉን እንዴትስ መረጥን
እራሱ ክርስቶስ ለኛ ያስተማረን
ለፍቅር መገዛት መተው ቂም በቀልን
ምን የቀረው አለ ለኛ የያልሆነልን
መንገዱ መልካም ነው የክርስትና ህይወት
በንስሃ ታጥበን ለስጋ ወደሙ ስንቀርብ በአንድነት
መምጫውን ስለማናውቅ ያ የማይቀረው ሞት
የዓለም ጣጣ አያልቅም ተዉ እንጨነቅ ለሰማያዊው ቤት
ኧረ የፍቅር ያለህ ፍቅር ጠፋ ወገን
መጨካከን በዛ ቀረ መተዛዘን
ጥንተ ጥላታችን በምድር ላይ ሲያናጥር
እርስ በርስ ሲያባላን ፍፁም ሳንጠረጥር
በሰዎች ጥላቻ በሰዎች ቅያሜ ከቤቱ ስንቀር
መንገዱን ስተናል ያላንዳች ጥርጥር
ባንድ ልብ እንጸልይ ቤተ እግዚአብሔር መጥተን
ኤሎሄ ይቅር በለን ሰላም ስጠን እያልን
ንጹህ ልብን ይዘን ከመጥን በፍቅር
የጥበብ ባለቤት ይሆናል ከኛ ጋር
ህሊናን ሰብስበን ጥቂት ብናስበው
ከሃይማኖት በላይ ሀብታችን ምንድነው
ቢከፋን ብናዝን የምንጸልይበት
የሃጢያትን ሰንኮፍ የምናወልቅበት
የክርስትናን ጣዕም የምንለይበት
በአርባ እና ሰማኒያ የተጠምቅንበት
በወላጆች እቅፍ መጥተን ያደግንበት
ቤቷን ብንሰራ ሆነን በአንድነት
የተዋህዶ ልጆች ስለምንከብርበት
ጸጋና በረከት ስለምናገኝበት
በምግባር እንጠንክር እንጽና በእምነት
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ስንዱ ተድላ
ሰላም ለኪ ማሪያም
ዓይኑ እያየ ታውሮ በራሱ ወጥመድ መራመድ አቅቶት ተዳክሞ
ተዝለፍልፎ ሲንገዳገድ ተሸንፎ
በእምነት ማጣት ባዶ ሆኖ ቀፎ
ትንቢት ሲደርስ ሲገጣጠም ሳይታይ ወረደለት
ሳይታሰብ ተፀነሰ ለደከመው ሊሆን ጉልበት
ከሰውነት ሥጋ አላብሰሽ ከደም ደም አዋርሰሽ
ለእኛ ስትይ መንገድ ሆነሸ
አሳልፎ እሱን ሰጥቶ ለእኛ አረገሽ
ይጠልቃል ይረቃል ይህ ሁሉ ሚስጥርሽ
ሰላም ለኪ ማሪያም ለክብርሽ
ሰላም ለኪ ድንግል ለፍቅርሽ
ሰላም ለኪ ኪዳነምኅረት
የንጽሕና ቅድስና መሠረት
የጽድቅ አክሊል የወርቅ ሙዳይ
አምሣያ የሌለሽ ከፍጥረታት በላይ
የሰማይ በር አምባ መጠጊያ ሆይ
በደሌን ትተሽው አድርጊኝ አገልጋይ
በዚያ በብርድ በግርግም ውስጥ የወለድሽው
እርጒም ሄሮድስ ሊያጠፋብሽ ሲያስፈልገው
ስደት ገብተሽ መከራውን ተቀብለሽ ያሳለፍሽው
አምላክ ሆኖ ጡት አጥብተሽ እንደ ሰው ልጅ ያሳደግሽው
በጐልጐታ ስትፀልዪ ስትማልጅው
እያነባሽ የልብሽን የነገርሽው
ልጄ ወዳጄ ሆይ! ጌታዬና አምላኬ
የምሻውን ሁሉ ትፈፅምልኝ ዘንድ፤ እጠይቃለሁኝ ይኸው ተንበርክኬ
መንገዱ እንዲሰፋ የሰው ልጅ መዳኛ
ስሜ ድልድይ ይሁን ካንተ መገናኛ
ቃል ኪዳን ግባልኝ ልቤም ደስ ይበላት
የጠፋችውን ዓለም መልሰህ አብጃት
እናቴ ሆይ አላት
ዘወትር ስንቅ አድርጐ ስምሽን ለሚጠራ
በንጹህ ኀሊና ቤትሽን ለሚሠራ
ስለ ማሪያም ሲባል ዕኩል ያካፈለ ከነዳያን ጋራ
ማሰብ አያሻውም ተዘጋጅቶለታል የፃድቃኖች ሥፍራ
በስምሽ ለሚያምን በዓልሽን ለሚያከብር
ቆሞ ላስቀደሰ አሽብሽቦ ለሚዘምር
ውዳሴ ተአምርሽን ገልጾ ለሚያስተምር
በእውነተኛው ቦታ ያገኘዋል ክብር
የተራበ አብልቶ ያጠጣ የጠማውን
አዝኖ ያለበሰ የተራቆተውን
ያዘነውን ሁሉ አፅናንቶ ያረጋጋ
ታማሚ እስረኛን ሲጠይቅ የተጋ
ተከፍቶ ያገኛል የሰማይ ቤት ዋጋ
የልቡንም መሻት ለአንቺ የነገረ
ምስልሽን በአንገቱ በቤቱ ያኖረ
ፀበልሽን የጠጣ ገብቶ የተነከረ
ሕይወቱ ፈውስ ነው በጣሙን ያማረ
ሰላም ለኪ ማሪያም ለክብርሽ
ሰላም ለኪ ድንግል ለፍቅርሽ
ሰላም ለኪ ኪዳነምኀረት
የንጽሕና ቅድስና መሠረት
በልጅሽ ቃልኪዳን መዳን እየቻልኩኝ
በሥምሽ ኋይል ብቻ ታምር እያየሁኝ
ምሥጋና ለማቅረብ ምነው ተሸነፍኵኝ
እመቤቴ ዳብሺኝ ዓይኔን ግለጪልኝ
ከሰይጣን ፍላጻ ከወጥመዱ እንድድን
አፋፍ ላይ ነኝና ዘርጊልኝ እጅሽን
ካላንቺ እርዳታ የለም እኮ መዳን
ግልፅ አርጐ ያስረዳል የልጅሽ ቃልኪዳን
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!
ለየካቲት ኪነምኅረት ዓመታዊ በዓል ተዘጋጅቶ የቀረበ
አዘጋጅና አቅራቢ ጌታሁን ዘውዴ ወ/ኪሮስ
የነበርን ዓይተናል
ቃልኪዳን ተከብሮ ታቦት አንግሰናል
የአባታችን ጸሎት በረከት ሆኖናል
የአባታችን ድካም ሰላምን ሰጥቶናል
ኦ! ማሪያም የአማኑአል እናት
የኪዳን ሕግ ጽላት
መስላለ መውጫ መንግሥተ ስማያት
ፍቅርን አልብስሽን ተነሳን ለጸሎት
ኅብረቀለም ምልክት እንዲሆንሽ
አምላክ ቃሉን አስተካክሎ አኖረልሽ
የሕይወት ፈውስ እንዲሆነው ለሚጠራሽ
በአባቱ በራሱ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃልኪዳን ገባልሽ
ማሪያም ብሎ ላከበረ ለዘከረ
ኃጥህ ሆኖ በላየስብ ለነበረ
በኪዳንሽ ነፃ ሆነ ሚዛን ደፋ ተቀየረ
እንደቃሉ እውነት ሆነ ፤ በእምነት መሰከረ
ከያሉበት መጡ ምዕመን ካህናት በቫንኮቨር ምድር
በኒውዌስት ሠፈር
በኆኀተ ስማይ ቅጽር
በኦርቶዶክስ ሥርዓት በዓልሽን ለማክበር
ቪክቶሪያ፤ ሲያትል፤ ላስቬጋስ፤ ሁሉም ተባበረ
ካህናት ምዕመን በዝቶልን ነበረ
የቆሙሱ ጸሎት መልሱ ተጀመረ
ፍቅርን ከኅብረት ጋር መሠረት አኖረ
አባቶች አስተማሩ ጠቃቅስው ወንጌሉን
አማኑኤል ለእናቱ ቃል የገባውን
የምሕረት መንገድ ጥርጊያውን
ጥንት የተጀመረ አሁንም ያለውን
የነበርን አይተናል ያልነበርን ሰምተናል
ቃልኪዳን ተከብሮ ታቦት አንግስናል
የአባታችን ጸሎት በረከት ሆኖናል
የአባታችን ድካም ስላምን ሰጥቶናል
በዕለተ ስንበት ቅዳሴው ሲቀደስ
በደመቀ ሁኔታ ተስጥዎ ሲመለሰ
የተሰበረ ልብ ምዕላውን ሲያደርስ
ማመልከቻው ሄደ እመንበሩ ድረሰ
አብሳሪሽ ገብርኤል ፤ ጠባቂሽ ሚካኤል
በፍጥነት ተገኙ አንቺን ለማገልገል
በመዝሙር በወረብ አድምቀው ውለዋል
አንድ ሁኑ እያሉ ፍቅርን ጋብዘውናል
ያልተነካ የለም የሁሉም ስሜቱ
እንዲያ ደምቆ ሲታይ ዐውደ=ምኀረቱ
ሁሉም ለበጎ ነው መሐረነ አቤቱ
ነገም ይደገማል እንደቸርነቱ
ደፋ ቀና ሲሉ እናቶች በጓዳ
ሰንበት ት/ቤት ሲያስተናግድ እንግዳ
ስበካ ጉባዔ ሁሉን ሲያስተባብር
ምእመን እንግዳ ሲስተናገድ በክብር
ቦታ አልበቃ ብሎ ማሳረፊያ ወንበር
አንተ ቅደም፤ አንቺ ቁጭ በይ ፤ እኔ ልቅር
ዓይተናል ደስ የሚል የኪዳኗ ፍቅር
ደስ የሚል የክርስቲያን ተግባር
ፈቃዱ ሆነና ታቦቱን ለማንገስ እኔም ስለነበርኩ
በዓይኔ በብረቱ ለማየትም ታደልኩ
ከደስታዬም ብዛት ምኞቴንም ቀጠልኩ
ምስሉንም እያየሁ ከልቤ ተማጸንኩ
ቸሩ ፈጣሪ ሆይ ! አቅሙ ስለሌለን
ለረጅም ዓመታት በኪራይ ቤት አለን
ስንዘምር በፍራቻ ድምጽ እየቀነስን
ስናከብርህ ተሳቀን ፤ ሥናነግስህ ተጨናንቀን
ከዚህ ሁሉ ችግር በቃችሁ በለን
አቤቱ ተለመነን!
እንደ ዳዊት ሳይሆን እንደ ሰለሞን ሆነን
ቅዱሱ ቤትህን ለማነጽ አብቃን
እንደ በደላችን ሳይሆን እንደ ቸርነትህ ይሁን
አሜን!
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!
አዘጋጅና አቅራቢ ጌታሁን ዘውዴ ወ/ኪሮስ